Faithlife Sermons

Untitled Sermon (7)

The Work and Word of the Cross  •  Sermon  •  Submitted
0 ratings
· 14 views

The Circumcision that is accomplished by the cross

Notes
Transcript
Sermon Tone Analysis
A
D
F
J
S
Emotion
A
C
T
Language
O
C
E
A
E
Social
View more →

ጌታችን በሥጋው ሰውነት ያከናወነው ግርዛት

“በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ”
ቆላስይስ 2፥11
“የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ”
ቆላስይስ 2፥11
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በመስቀል ላይ በሰራው ስራ መጠበቅ ያለበት ትልቅ መንፈሳዊ ምስጢር አለው። የመስቀሉን ስራ በመስቀሉ ቃል ካልጠበቅን በምንም አይነት ትክክለኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር አይቻልም። ጌታችን በመሥቀሉ ላይ የሰራው ስራ መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚነካ ነው። መስቀሉ የሐጢያት እዳ የተከፈለበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን የሐጢያት ምክንያት የሆነው ሥጋና በዚያ ሥጋ የሚኖር ፍጥረታዊና ምድራዊ የሆነ የሰው ማንነት የተወገደበትና የተሰቀለበት ስፍራ ነው። ከላይ ያነበብኩላችሁ የጌታ ቃል የሚናገረው ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለማዳን ካደረጋቸው ስራዎቹ መካከል ዋና ከሆኑት ነገሮች አንዱን ነው። ጳውሎስ የሚለውን ልብ ማለት ይገባናል።
በዚህ መሪ ሃሳብ ውስጥ የሚናገረው ጌታችን የሰራው ስራ ምን እንደሆነ በቅርበትና በጥልቀት መመልከት አለብን። ጳውሎስ ስለ መገረዝ ይናገራል። መገረዝ ምን ማለት ነው? የእግዚአብሔር ሕዝብነት መለኪያና መመዘኛ ነው። አይሁዳውያን ታሪካቸው የተጀመረውና የተደራጀው አብርሃም ይስሐቅን በዘፍጥረት 21፥4 ላይ ከገረዘው በኋላ እንደነበር ያምናሉ። መገረዝ ለአይሁዳውያን የቃል ኪዳን ህዝብ የመሆናቸው ምልክት ነው። ጌታ አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን በገባበት ግዜ በዘፍጥረት 17፥10 ላይ “በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ” በማለት እንዳዘዘው እናያለን። ይህ ለልጅ ልጅ የተሰጣቸው ስርዓት የእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕዝብነቱ መለያና መመኪያ ሆኖላቸው እንደኖሩ እንመለከታለን። በመገረዝ የእግዚአብሔር ሕዝብነትን ምልክት መቀበል ነው። ይህ ጉዳይ በእስራኤላውና ታሪክ ጎልቶ የሚታይ እንደነበር በብዙ ሁኔታ የሚታይ ነው። ሙሴ እስራኤልን ነጻ ሊያወጣ ወደ ግብጽ በሄደበት ግዜ ልጁን ሳይገርዘው በመቆየቱ እግዚአብሐር ሊገድለው በመንገድ እንዴት እንደተገናኘው እናያለን። “እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። 25 ፤ ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፥ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው። አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች። 26 ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ። ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች” ዘጸ. 4፥24-26 መገረዝ የቱን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል የቃል ኪዳን ምልክት እንደሆነ እንመለከታለን።
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አይሁዳዊነቱ ሲያወራ የማንነቱ መለያ አድርጎ የወሰደው አንዱና ትልቁ ነገር በስምንተኛው ቀን መገረዙን በመጥቀስም ነበር። በፊልጵስዩስ 3፥5 ላይ “በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ” የሚለው ቃል ይህንን ያሳያል።
አይሁዳውያን ከግብጽ ምድር የወጡበትን የፋሲካን በአል ማክበር የሚችሉት የተገረዙ ከሆኑ ብቻ ነው። ያልተገረዘ ሰው ያንን በዓል ፈጽሞ ሊያከብር አይችልም። በዘጸአት 12፥48 ላይ “እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ” የሚለው መመሪያ በጽኑ የሚጠበቅ የአምላክ ትእዛዝ እንደነበር እንመለከታለን።
ያልተገረዘ ህዝብ እግዚአብሔር ተስፋ ወደገባለት በረከትም አይገባም። እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር ሲወጡ ሁሉም ተገርዘው ነበር። ፋሲካን ያከበሩ ሁሉ ተገርዘው ስለነበር ከግብጽ ምድር የወጡት ሁሉ የተገረዙ ነበሩ። ነገር ግን ከብግስጽ ምድር ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ የተወለዱት አይሁዳውያን የተገረዙ አልነበሩም። ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ በነበሩበት ሰዓት እግዚአብሔር ኢያሱን በምዕ. 5፥2 ላይ “የባልጩት መቍረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው አለው” በማለት ሲያዘው እናያለን። በቁጥር 3 ላይ “ኢያሱም የባልጩት መቍረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ” የሚል ቃል እናያለን። የግርዛት ኮረብታ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ገባላቸው ምድር ለመግባት የሚያስችላቸው ሁኔታ የተካሄደበት ስፍራ ነበር። በግርዛት ኮርብታ ላይ አይሁዳውያኑ ከተገረዙ በኋላ በቁጥር 9 ላይ “እግዚአብሔርም ኢያሱን። ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው” ከዚህ የተነሳ “የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ”

መገረዝ የግብጽ ነውር ማነከባለያ የሆነበት መንፈሳዊ ምስጥሩ እምን ላይ ነው ያለው?

ጌልጌላ በእብራይስጥኛ “ጊልጋል” ማለት ማንከባለል ማለት ነው። መገረዝ ነውር ማንከባለያ የሆነበት ምክንያትና ምስጢሩ ምንድር ነው? በሰው ስጋ ላይ የሚደረገው ግርዛት የልብ ግርዛት ምልክት ነው። የግብጽ ነውር በእስራኤላውያን ብጥቅሌ ሥጋ ላይ አይደለም። የግብጽ ነውር ያለው በልባቸው ነበር። መገረዝ የሚያሳየው የልብን ግርዛት ካልሆነ መገረዝ አለገመገረዝ ይሆናል። ሙሴ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ምክር በቅጡ የተረዳ ታላቅ መሪ ነበር። አይሁዳውያኑ ሲገረዙ የኖሩትን የስጋ መገረዝ የሚበልጠውን የልብ መገረዝ ይናገራቸዋል። በዘዳግም 30፥6 ላይ “በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል” ሙሴ እግዚአብሔር ያደርገዋል ያለው ይህ የልብ መገረዝ አይሁዳውያኑ በስጋቸው ላይ ሲያደርጉት ከነበረው መገረዝ የሚበልጥ መገረዝ እንደሆነ ያመለክታቸዋል። በአምላክ የሚከናወነደው ይህ መገረዝ በሰው ልብ ውስጥ የሚካሄድ እንደሆነም ያሳያቸዋል። የሰው ልብ የክፋትና የሐጢያት ምንጭ የሆነ ስፍራ ነው። የሰው ልብ በእግዚአብሔር ሲገረዝ ሰው እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ የሚወድና የሚታዘዝ ይሆናል። ይህንን የልብ መገረዝ ሳያገኙ አይሁዳውያን በስጋቸው ላይ በተደረገ የስጋ ስርዓት ብቻ በመመካት ልባቸው ከአምላካቸው ጋር የተጣላና ያልተጣጣመ እየሆነ ይኖሩ ነበር።
የልብን መገረዝ አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 2፥28-29 ላይ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “28 በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ 29 ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም” አይሁዳውያኑ ከእግዚአብሐር የተቀበሉት በሥጋቸው ላይ የሚደረገው መገረዝ የልብ መገረዝን አመልካች ሆኖ ይህንን የልብ ግርዛት የሚያደርገው እግዚአብሔር እንደሆነ ሲያሳያቸው የነበረውን መቀበልና መረዳት ይቸገሩ ነበር። ልባቸው ሳይገረዝ በሥጋቸው ግርዛት ብቻ ይመኩ ነበር። የልብ ግርዛት የሚያስጥለውን ሥጋዊ ትምክህት የሥጋ ግርዛት እያራመዱ ይኖሩ ነበር። ከሥጋ ትምክህት የሚያስጥለውን የልብ ግርዛት ምልከት ሥጋዊ ለሆነ ትምክሕት ተጠቀሙበት። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ይህ ትክክል እንዳለሆነ ለማሳየት ነበር የሚናገራቸው። “28 በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ 29 ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም”። እንዲህ የመሰለውን እውነት ነቢያት ለእስራኤል ሕዝብ ሲናገሩ ነበር የኖሩ። ኤርምያስ በምዕራፍ 9፥25 ላይ “አሕዛብ ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና የተገረዙትን ሁሉ፥ ግብጽንና ይሁዳን ኤዶምያስንም የአሞንንም ልጆች ሞዓብንም በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጕራቸውን በዙሪያ የተላጩትን ሁሉ፥ ባለመገረዛቸው እነርሱን የምቀጣበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር” እያለ ተገርዣለሁ የሚሉትን አይሁዳውያን ካተገረዙት አሕዛብ ጋር የሚቀጣበት ዘመን እንደሚመጣ ያስጠነቅቃቸዋል። የስጋ ግርዘት በማግኘታቸው የሚመኩትን አይሁዳውያንን ልባቸው ባለመገረዙ በሥጋቸው ካተገረዙት አሕዛብ ጋር አንድ አድርጎ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው በራሳቸው ነቢያት መናገሩ ድንቅ ነገር ነው። መገረዝ የልብን ግርዛት ካላመጣ ያንን እንዲሹና እንዲፈልጉ ካላደረገ ምንም ጥቅም እንደሌለው እናያለን። መገረዝ እንዳለመገረዝ እንደሚቆጠር ይታወቃል።
በአዲስ ኪዳን ስንመጣ መገረዝ በመሲሁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተካሄደ አዲስ ኪዳን ያስተምረናል። ግርዛትን እስመልክቶ በአዲስ ኪዳን ስንመለከት የብሉይ ኪዳኑ ስጋዊ መገረዝ በአዲስ ኪዳን ለማድረግ የፈለጉትን ብሉይን ከሐዲስ በመቀየጥ የሥጋ ትምህትን ሊያመጡ የሚወዱ መናፍቃን የወንጌል እንቅፋቶች የተነሱበት ግዜ ነበር። ይህንን ሁኔታ ጳውሎስ እንዴት እንደተቋቋመው ለመመልከት ምንም ሰው ለገላትያ ሰዎች የጻፈውን መጽሐፍ ብቻ ቁጭ ብሎ ቢያነበው ሊረዳው የሚችለው ጉዳይ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥቀሉ ላይ ያደረገውን ግርዛት ያላወቁና የማያስተውሉ ሰዎች መገረዝን የሚሹበትም ምክንያት ጳውሎስ ሲናገር የተናገረውን ልብ ማለት ይገባናል። በገላትያ 6፥12 ላይ “በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው” ያለውን ሐዋርያው እውነት መመልከት ይገባናል። በሥጋ የሚሆነው የብሉይ መገረዝ ከፍ ብዬ ባነበብኩት ቃል እንዳየነው “መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም” የሚለው የልብ መገረዝ በሥጋ የማያስመካ መገረዝ ነው። ይህ መገረዝ ከሥጋዊ ትምክሕት ጋር የተጣላ ነው። በልብ መገረዝ ትሕትናን በእግዚአብሔር መመካትን ያመጣል እንጂ ሥጋዊና ምድራዊ ትምክህትን አያመጣም። እኛ እንዲህ አድርገናል፣ እኛ እንዲህ ሆነናል የሚያስብል ትምክህትና ጉራን አያስቸረችርም። የእስራኤልን ሕዝብ ከመቀጣት ያላዳነው የብሉ ኪዳኑ መገረዝ በፍርድና ኩነኔ ከሚያድነው ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጋር ተቀላቅሎ አይሰበክም። እንዲህ ማድረግ ትልቅ ስሕተትና ምንፍቅና ነው። ለምን? ሐዋርያው በአዲስ ኪዳን በኢየሱስ ደም የተዋጁትን ተገረዙ እያሉ የሚሰብኩ የመገረዝ ወንጌል ሰባኪዎች ይህንን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ጳውሎስ ሲናገር ያለው “በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም” የሚል ነው። ሕግን የማይጠብቁ ግን በመገረዛቸው የሚመኩ እኛ ተገርዘናል እናንተም ተገረዙ የሚሉት የራሳቸውን የሥጋ ትምክህት ለመጠበቅ ሲሉ ነው። በሰው ሥጋ ላይ በሚደረግ መገረዝ እከሌን ገረዝኩት፣ አከሌን እስገረዝኩት በማለት ትምክህት ፈላጊዎች ናቸው። ይህ በአዲስ ኪዳን ለምን የማይፈለግ ክፉ የሆነ የተረገመ ትምህርት ሆኖ ተወሰደ? ጳውሎስ ለዚህ መስል ሲሰጥ በገላትያ 6፥14-16 ላይ እንዲህ ይላል፦ “14 ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። 15 በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 16 በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን” ጳውሎስ ምንድር ነው የሚለው? መገርዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም ማለት ምን ማለት ነው? መገርዝን ካለመገረዝ ጋር አንድ ያደረገው የአዲስ ኪዳን ወንጌል ከምን የተነሳ ነው? አዲስ ኪዳን ነገሩ ሁሉ ያለው ጌታችን በመሥቀሉ ላይ በሰራው ስራ ላይ ያረፈና የተመሰረተ ነው። መስቀሉ ብሉይ ሊያስወግደው ያልቻለውን ሐጢያት ጌታችን ደሙን ያፈሰሰበት ስራ የተሰራበት ስፍራ ነው። መሥቀሉ ጌታችን ሐጢያትን ያስወገደበት ስፍራ ብቻ አይደለም። ሐጢያት የሚያሰራችንን ሥጋ የሰቀለበት ስፍራ ነው። መስቀሉ ሐጢያተኛው ለሰራው ሐጢያት ብቻ ጌታችን የሞተበት ስፍራ አይደለም። መሥቀሉ ጌታችን ሐጢያተኛው ለሐጢያት እንዳይኖር በሞት ሐይል ከሐጢያት ተለይቶ ለእግዚአብሔር እንዲኖር ለሚያደርገው ለትንሳኤ ሕይወት ሐይል ብቁ እንዲሆን የበቃበት ስፍራ ነው። መስቀሉ ብሉይ በብጥቅሌ ሥጋ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሲያደርግ መስቀሉ ግን ሐጢያተኛውን ለሐጢያት እንዲሞት በማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ሕይወት ሐይል ለእግዚአብሔር እንዲኖር በማድረግ ሰው ከዓለምና ከምድራዊ ሕይወት የሚገላገልበት የተካሄደበት ነው።
የመስቀሉ ጠላቶች በሥጋ የሆነ ትምክሕትን የሚያራምድ፥ በምድራዊ ቅራቅንቦና በሥጋዊ ምኞት የሚሞላ ስብከት ይሰብካሉ። የመሥቀሉ ጠላቶች የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ ጌታችን ሰውን ከዓለም ዓለምንም ከሰው የለየበትን የመሥቀሉን ሐይልና ስራ ዋጋ በሚያሳጣ መለኮታዊ ትምክህት የሚያስገኘውን ቃል በመሽቀጥ ያገለግላሉ። የመስቀሉ ቃል ጠላቶች ስራቸውን በዚህ በመሥቀል ቃል አግዚአብሔር ይፋለማቸዋል።
በመግቢያ ላይ ያነበብኩላችሁ የጌታ ቃል በቆላስይስ 2፥11 እንደሚያሳየን “በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ” በቀድሞው ትርጉም ዀ“የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ”
ቆላስይስ 2፥11
Related Media
Related Sermons